Psalms 27

ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ሰው ድፍረት

የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኅኔ ነው፤
የሚያስፈራኝ ማን ነው?
እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤
ማንን እፈራለሁ?

2ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ፣
ወይም ስሜን ሊያጠፉ

ክፉዎች ገፍተው በመጡ ጊዜ፣
ጠላቶቼና ባላጋራዎቼ በተነሡብኝ ጊዜ፣
እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ።
3ሰራዊት ቢከብበኝ እንኳ፣
ልቤ አይፈራም፤
ጦርነት ቢነሣብኝ እንኳ፣
ልበ ሙሉ ነኝ።

4 እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤
እርሷንም እሻለሁ፤
ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣
በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣
የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣
በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
5በመከራ ቀን፣
በድንኳኑ ውስጥ ይሰውረኛልና፤
በድንኳኑም ጓዳ ይሸሽገኛል።

6በዚህ ጊዜ በዙሪያዬ ባሉ ጠላቶቼ ላይ፣
ራሴ ከፍ ከፍ ይላል፤
በድንኳኑም ውስጥ የእልልታ መሥዋዕት እሠዋለሁ፤
ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፤
እዘምርለታለሁም።

7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ስማኝ፤
ራራልኝ፤ ስማኝም።
8“ፊቴን ፈልጉ” ባልህ ጊዜ፤
ወይም ልቤ ሆይ፤ ለአንተ “ፊቴን” አለ

ልቤ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊትህን እሻለሁ አለች።
9ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤
ተቈጥተህ አገልጋይህን አታርቀው፤
መቼም ረዳቴ ነህና።
አዳኝ አምላኬ ሆይ፤
አትጣለኝ፤ አትተወኝም።
10አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣
እግዚአብሔር ይቀበለኛል።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤
ስለ ጠላቶቼም፣
በቀና መንገድ ምራኝ።
12ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ፤
የሐሰት ምስክሮች ተነሥተውብኛልና፣
ዐመፃ የሚረጩ ናቸው።

13 የእግዚአብሔርን ቸርነት
በሕያዋን ምድር እንደማይ
ሙሉ እምነቴ ነው።
14 እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤
አይዞህ፣ በርታ፤
እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።
Copyright information for AmhNASV